ገበያን መፈለግ ወይስ ገበያን መፍጠር?

ገዝተህ መልሰህ የምትሸጥ ከሆነ ነጋዴ ትባላለህ። ነጋዴ ባትሆንም ግን መኖር፣ ማደግ፣ ስኬታማ መሆን ከፈለግክ ሰጥተህ መቀበል አለብህ። ህይወት ልውውጥ (Transaction) ናት። የምትሸጠው ነገር ሊኖርህ ይገባል። እውቀት ካለህ እውቀትህን ትሸጣለህ፣ ጉልበት ካለህ ጉልበትህን ትሸጣለህ፣ ጊዜ ካለህ ጊዜህን ትሸጣለህ፣ የምታመርተው ነገር ካለህ ያመረትከውን ትሸጣለህ፣ . . .ወዘተ። ወይም የሆነ ነገር ትገዛና አትርፈህ ትሸጣለህ።

ይህ ከሆነ ስኬታችን (ተወደደም ተጠላ) በምንሸጠው ነገር፣ በምንሸጠው መጠን፣ በምንሸጠው ዋጋ፣ እና በመሳሰሉት ይወሰናል። ለዚህ ነው የማርኬቲንግ ጥበብ ከሁሉም በላይ ወሳኝ የሚሆነው። ተራራ የሚያክል ምርት ቢኖርህ መሸጥ ካልቻልክ ትርጉም የለውም። እውቀት ያግበሰበስክ ሊቅ ብትሆን እውቀትህን መሸጥ ካልቻልክ ሸክም ብቻ ነው የምታተርፈው። ጥበብ ኖሮህ ጥበብህን መሸጥ ካልቻልክ ተመፅዋች ከመሆን አትድንም።

ወዘተ…ወዘተ

ለመሸጥ ገበያ ያስፈልግሃል። ገበያ ማለት ገዢ ነው። ገበያ በሁለት መንገድ ታገኛለህ። ወይ ያለውን ገበያ ፈልገህ ታገኘዋለህ። ወይ አዲስ ገበያ ትፈጥራለህ። ያለውን ገበያ መፈለግ ቀላሉ መንገድ ቢሆንም የተገደበ እና ውድርር የበዛበት ነው። ስለዚህ የበለጠ ውጤታማ መሆንና ገደብ የለሽ ዕድል ማግኘት ከፈለግክ ገበያን መፈለግ ሳይሆን ገበያን መፍጠር ነው ያለብህ፡፡ የዛሬው ርእሳችንም ይሄው ነው።
ገበያን መፍጠር ምን ማለት ነው?

ይህን በምሳሌ እንየው፡

አንተ አስጎበኚ ድርጅት ነው ያለህ እንበል። ላሊበላን እናስጎበኛለን ብለህ ማስታወቂያ ለጥፈሃል፣ አስነግረሃል፣ በሶሻል ሚዲያ ሼር አድርገሃል … ። ይህንን ስታደርግ ገበያ እየፈለግክ ነው። ይህ ምን ማለት ነው? አዲስ አበባ ውስጥ ላሊበላን መጎብኘት የሚፈልጉ በአመት በአማካይ 1,000 ሰዎች አሉ ብለን እናስብ እና ላሊበላን የሚያስጎብኙ 30 ድርጀቶች አሉ እንበል። አንተ ገበያ እየፈለግክ ያለኸው ከ30ዎቹ ድርጀቶች ጋር ለመቀላቀልና ከ1000ዎቹ ሰዎች የተወሰነ ድርሻ ለማግኘት ነው። ይህ መጥፎ አይደለም። ግን ከዚህ አጥር መውጣት እየቻልክ ለምን በዚህ ትገደባለህ? ገበያውን ለምን ራስህ አትፈጥረውም?

ለምሳሌ እንዲህ ብታደርግ፡- በኮሌጆች ተማሪዎች በጋራ ላሊበላን እንዲጎበኙ የሚያስተባብር ነገር ለምን አትፈጥርም? የተቋቋሙ ክበባት ጋር ሃሳቡ እንዲነሳ ለምን አታደርግም? የመስሪያቤት ሰራተኞች የጉብኝት ፕሮግራም ለምን አታስተባብርም? የተለያዩ ዘርፍ ሰልጣኞች የስልጥናቸው ማጠቃለያ የላሊበላ ጉብኝት እንዲሆን ለምን አታስተባብርም? ስለ ላሊበላ ውበትና አስገራሚነት የሚተርክ ሳቢ የሆነ ቪዲዮ ሰርተህ ከአንተ አድራሻ ሊንክ ጋር ለምን ሼር አታደርግም?…

 እነዚህን በማድረግህ ከ1000ዎቹ ሰዎች ውጪ የሆነ አዲስ ገበያ ፈጠርክ ማለት ነው።

የአቮካዶ ምርት አቅራቢ ብትሆን የአቮካዶ የምግብ ተፈጥሮአዊ ይዘት (Nutritional Value) በሚስብ መልኩ የሚገልጹ የቪድዮ፣ የጽሁፍ፣ የድምጽ ፕሮግራሞችን ሰርተህ ለምን ሼር አታደርግም? ወይም ድረ-ገጽ ቀርጸህ በአቮካዶ ላይ ቋሚ blog ለምን አይኖርህም? እንደዚህ ብታደርግ አዳዲስ የአቮካዶ ተመጋቢዎችን ትፈጥራለህ። ይህም ማለት አዳዲስ ገዢዎችን (አዳዲስ ገበያዎችን) ፈጠርክ ማለት ነው።

አዲስ ገበያ መፍጠር ማለት ግን እንዲህ ብታደርግ እንዲያ ብታደርግ ተብሎ የሚታለፍ አይደለም። ራሱን የቻለ የፈጠራ ስራ ነው። ስለዚህ አእምሮህን አሰራውና አዲስ ፈጠራ ተጠቅመህ አዲስ ገበያ ፍጠር። ገበያን በመፍጠር ብቁ ከሆንክ በርግጠኝነት ባለህ ነገር ላይ ውጤታማ ትሆናለህ።
Harvard Business Review መጽሄት ላይ የወጣ ጽሁፍ እንዲህ ይላል: “Creating new market requires a different pattern of strategic thinking.”

በነገራችን ላይ አዲስ ገበያን መፍጠር በተለየ አንግል የማሰብ ብቃትን ይጠይቃል።
በቀጣይ በተለያዩ ዘርፎች ላይ ገበያን ስለመፍጠር በምሳሌ እየወሰድን ለማየት እንሞክራለን።  

ድረ-ገጻችንን ጎብኙ።www.alhabaccounting.com ስለምንሰጣቸው አገልግሎቶች ማብራሪያ ለማግኘት በ 0911232322 ይደውሉ።

1 thought on “ገበያን መፈለግ ወይስ ገበያን መፍጠር?”

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *